ወሮታ ለፍትሕ ስለ አህመድ ዲሪዬ በሌላ ስሙ አህመድ ኡመር እና አቡ ኡባይዳህ ተብሎ ስለሚታወቀው ግለሰብ መረጃ ለሚሰጥ እስከ $10 ሚሊዮን ወሮታ ይከፍላል፡፡ አቡ ኡባይዳህ የአል-ሸባብ መሪ በመሆን በማገልገል ላይ ሲሆን፣ ይህንንም የመሪነት ስፍራ የአል-ሸባብ መሪ አህመድ አብዲ ጎዳኔ ከዚህ አለም በሞት ከተለየበት ጊዜ ጀምሮ ይዞ ቆይቷል፡፡ አቡ ኡባይዳህ ጎዳኔ በሞተበት ጊዜ ከጎዳኔ የቅርብ ሰዎች መካከል አንዱ ነበር፡፡
አቡ ኦባይዳህ ጎዳኔን ከመተካቱ በፊት በአል-ሸባብ ውስጥ በተለያዩ ቦታዎች አገልግሏል፤ ከእነርሱም መካከል የጎዳኔ ረዳት፣ በ2000 ዓ.ም. የሶማሊያ የታችኛው ጁባ ክልል ምክትል አስተዳዳሪ እና የአል-ሸባብ የሶማሊያ ቤይ እና ባኩል ክልሎች አስተዳዳሪ በመሆን በ2001 ዓ.ም. አገልግሏል፡፡ በ2005 ዓ.ም. የጎዳኔ ከፍተኛ አማካሪ እና የአል-ሸባብ “የውስጥ ክፍል” በመሆን ሰርቷል፤ በዚህም የቡድኑን የአገር ውስጥ እንቅስቃሴዎች ይመራ ነበር፡፡ ይህ ግለሰብ ከጎዳኔ ጋር አል-ሸባብ በአል-ቃዒዳ ታላቅ አለም አቀፋዊ እቅዶች ውስጥ በሶማሊያ ለማድረግ የታቀዱትን የሽብር ጥቃቶች የሚጋራ ሰው ነው፡፡
በሚያዝያ 13 ቀን 2007 ዓ.ም. የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አቡ ኡባይዳህን ልዩ አለምአቀፍ ሽብርተኛ በማለት በስራ አስፈፃሚ ትእዛዝ (ኤክዘኪውቲቭ ኦርደር) 13224 እንደተሻሻለው መዝግቦታል፡፡ በዚሀም መሰረት በዩናይትድ ስቴትስ አስተዳደር ወሰን ውስጥ የሚገኙ የአቡ ኡባይዳህ ንብረቶች እና ጥቅሞች ሁሉ ታግደዋል፣ ማናቸውም የዩናይትድ ስቴትስ ሰዎች ከአቡ ኡባይዳህ ጋር በምንም አይነት ልውውጥ ላይ መሳተፍ አይፈቀድላቸውም፡፡ በተጨማሪም በዩናይትድ ስቴትስ በውጭ አገር የሚገኝ ሽብርተኛ ድርጅት በሚል ለተመዘገበው አል-ሸባብ ድርጅት ሆን ብሎ የማቴሪያል ወይም የሀብቶች አቅርቦት ማድረግ፣ ወይም ለማቅረብ መመሳጠር የተከለከለ ወንጀል ነው፡፡